ብሔርተኝነት
ብሔርተኝነት የፖለቲካ ርዕዮት ዓለም ሲሆን መሪ ሐሳቡ የአንድ ግለሰብ ታማኝነት ከሁሉ ዓይነት የግል ወይንም የቡድን ፍላጎት በላይ ለብሔሩ ወይንም ለብሔረ መንግስቱ ነው የሚል ነው። ስለሆነም ብሔርተኝነት የብሔርን ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና በተለይ ደግሞ ምጣኔ ሃብታዊ ጥቅም ለማሳደግ የሚጥር ሥርዓት ነው። ብሄርተኝነት አንድ ብሄር ከተጋረጠበት የህልውና አደጋ ራሡን ለማዳን የሚጠቀምበት የፖለቲካ ርዮት አለም ነው።
ብሔርተኝነት በ18ኛው ክፍለ ዘመን በአውሮጳ ዘንድ የተፈጠረ፣ በኋላም በሃያኛው ክፍለ ዘመን ወደ እስያና አፍሪካ የተስፋፋ እንቅስቃሴ ነው። ከ18ኛው ክፍለ ዘመን በፊት፣ በብዙ ምክንያቶች፣ አውሮጳዎች የብሔራዊ ስሜት አልነበራቸውም። ተገዥነታቸውም በአካባቢያቸው ላለ ርስት ጉልተኛ ከዚያም ካለፈ ለከተማ መንግስት ወይንም ለዘውጋዊ አገዛዝ ወይንም ለሃይማኖታዊ ሥርዓት ነበር። ፖለቲካዊ ታማኝነታቸው ለብሔራዊ መንግስታቸው ስላልነበር፣ ሥልጣኔ የብሔር ሳይሆን ፣ ዓለም ዓቀፋዊ ነው የሚል ግንዛቤ ነበራቸው።
በዚህ ወቅት ከሞላ ጎደል ማህበረሰቡ በግብርና የሚተዳደር ነበር። ሠራተኛው መደብ ብዙውን ጊዜውን በጉልበት ሥራ ላይ ስለሚያሳልፍ፣ እንደ መሳፍንት-መኳንንቱና ጻሕፍት-ደብተራዎቹ ጊዜ አግኝቶ ለማንበብና ለመጻፍ ስለማይችል፣ በሁለቱ መደቦች መካከል የነበረው የዕውቀት ልዩነት ከፍተኛ ነበር። ስለዚህ ዕውቀት የውሱኖች እና ለውሱኖች ስለነበር፣ አብዛኛው ማህበረሰብን የሚያሳትፍ ሐሳብ ሊገኝ አልተቻለም። ብሔርተኝነትም በተፈጥሮ የማይገኝ የሐሳብ ዓይነት እና በትምህርት የሚኮለኮል እንደመሆኑ፣ እንዲሁም አብዛኛውን ሕብረተሰብ ካላሳተፈ ትርጉም ስለሌለው በዘመኑ ሊፈጠርም ሆነ ሊያብብ አልቻለም። ሐሳቡን ለማፈለቅ እሚችሉት የኅብረተሰብ መደቦችም፣ ከቁጥራቸው ማነስ የተነሳ ከተለያዩ የአውሮጳ ጻሕፍት ምሁራን ጋር በጊዜው ዓለም ዓቀፍ በነበሩት የግሪክ እና ላቲን ሥልጣኔዎች ላይ ተመርኩዘው ዓለም ዓቀፋዊ (ወይንም አውሮጳ አቀፋዊ) ማንነትን በመያዝ የተጠመዱ እንጂ ለበታች ተገዥዎቻቸው ዕውቀትን ለማካፈል ምንም የሚገፋፋቸው የራስ-ጥቅም አልነበራቸውም።
በ18ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ በአውሮጳ ውስጥ የኢንዱስትሪ መስፋፋት በነባራዊው የመደብ ክፍፍል ላይ ከፍተኛ ለውጥ አስከተለ። ይህን ኢንዱስትሪያዊ ኤኮኖሚ ለማካሄድ የግዴታ ብዙ የተማረ ሰው አስፈለገ። የተማረ ክፍል በበዛ ቁጥር፣ በዚያው ልክ ከሩቅ አገር አውሮጳውያን ጋር በደብዳቤና በመጻህፍት ሐሳብ ከመለዋወጥ ይልቅ በቅርበት እርስ በርስ መለዋወጥ ቀላል ሆኖ ተገኘ። አንድ ሰው፣ በአለም አቀፋዊ ቋንቋዎች (ለምሳሌ ግሪክ እና ላቲን) ሳይሆን በቅርቡ በሚገኝ በአፍ መፍቻ ቋንቋው መማር ጀመረ። ይህም ቀስ በቀስ ፣ ሥልጣኔ በብሔር እንደሚዎሰን ግንዛቤ አመጣ። የዚህ የትምህርት ብሔርተኝነት፣ የገዥውንም ሆነ የተገዥውን መደብ አንድ የሚያረግ፣ ስለሆነም ሁለቱን መደቦች በአንድ ማንነት፣ በብሔራቸው የሚያስተሳስር ስለሆነ፣ ከፖለቲካዊ እና መንግስታዊ ብሔርተኘነት ጋር እያደገ ሄዶ በስተመጨረሻ በአውሮጳ ውስጥ ብዙ ለውጦችን አስከትሏል። ከነዚህም ውስጥ፣ የኦቶማንና የአውስትሮ-ሃንጋሪ የዘውግ ሥርዓት መፈረካከስ፣ የጣሊያን እና ጀርመን ብሔረ-መንግስታት መመስረት፣ በኋላም የአንደኛው ዓለም ጦርነት መነሳት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የዚህ ርዕዮት ውጤቶች ናቸው።
ምንም እንኳ ዘመናዊ ብሔርተኝነት ከላይ እንደተገለጸው በአውሮጳ 18ኛው ክፍለ ዘመን እንደተፈጠረ በብዙ የፖለቲካ አጥኝዎች የታመነ ቢሆንም፣ አንድ አንዶች ብሔርተኝነት የተፈጠረ ሳይሆን ምንጊዜም በተፈጥሮ ያለ ነው ይላሉ። ስለሆነም ብሔርተኝነት በሁለት ይከፈላል። የመጀመሪያው አይነት ብሔርተኝነት፣ ዜጋዊ ብሔርተኝነት ሲባል የምዕራባዊ አውሮጳ ብሔርተኝነት በመባል ይታዎቃል። ሁለተኛው እና ተፈጥሮዓዊ ነው የሚለው ደግሞ ብሔረሰባዊ ብሔርተኝነት ይባላል። ብሔረሰብ እዚህ ላይ ከብሔርን ይልቅ ጎሳን ያመላክታል።
ብሔርተኝነት በአሁኑ ዘመን እጅግ ከፍተኛ ኃይልና ፋይዳ ያለው የፖለቲካ ርዕዮት ነው። ሥለሆነም በሰፊው በተላያዩ ተቋሞች ይጠናል።
ጅምር! ይህ አጭር ጽሑፍ መሠረት ወይም መዋቅር ነው። አሁን ሊያስፋፉት ይችላሉ! |